የኢሚግሬሽን፣ ስደተኞችና ዜግነት ሚኒስትር በኢ/ያ ማህበር በቶሮንቶና አካባቢው ጽ/ቤት

የኢሚግሬሽን ስደተኞችና ዜግነት ሚኒስትር የተከበሩ ማርክ ሚለር በኢትዮጵያ ማህበር በቶሮንቶና አካባቢው ጽሀፈት ቤት አርብ ኦክቶበር 27 ቀን 2023 በመገኘት ከኢትዮጵያ ማህበር የቦርድ አባሎች ጋር ሰደተኞችን በሚመለከት መነጋገራቸውን የማህበሩ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ።

ክቡር ሚኒስትሩን አጅበው የመጡት የተከበሩ የፓርላማ አባል ማይክል ኮቱ፤ እንዲሁም የሚኒስትሩ ረዳት እና ሚስተር ብሩስ ዴቪስ የማህበረሰብ እድገት ፕሮጄክት ማኔጅመንት አማካሪ (በሎካል ዩኒየን በኩል የመጡ) መሆናቸውም ታውቋል።

በማህበሩ ጽሀፈት ቤት አዳራሽ ተገኝተው የተወያዩበት ዋና ዓላማ፤ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቶሮንቶ ከተማ ከፌዴራልም ሆነ ከሲቲው ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታ በሚገባ ባለማግኝታቸው፤ የኢትዮጵያ ማህበር በቶሮንቶና አካባቢው ከሜይ 2023 መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ፒተር ስትሪት መጠለያ አጥተው በራፍ ላይ ሲንገላቱ የነበሩትን ስደተኞች በማምጣት የሚቻለውን እርዳታ ሲያደርግ ቆይቷል። ስድተኞቹ መጠለያ እስኪያገኙ ድረስ በየሆቴሉ በማሳረፍ፣ እንዲሁም ቶሮንቶና ኤጃክስ ቤቶችን ተከራይቶ አስር እና አስራ አምስቱን አንድ ላይ በማኖር፣ የስደተኛነት ጉዳያቸውን በጽሀፈት ቤቱ የመንግስት ማመልከቻዎችንና የጠበቃ ጉዳያቸውን እንዲያሟሉ በማድረግ፣ ህበረተሰቡም ባደረገው ትብብር በጽህፈት ቤቱ አዳራሽ ምግብ በመመገብ እና ወደ መጠለያቸው ሲጓጓዙም የትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን እየረዳ መቆየቱን በሚገባ በማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰረት ደመቀ የተገለጸላቸው ሲሆን፤ የዶንቫሌይ ኢስት አካባቢም የፓርላማ አባል የተከበሩ ማይክል ኮቱ እና ሚስተር ብሩስ ዴቪስ በተጨማሪ በሚገባ ለሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ማህበር ከአቅሙ በላይ የሆነ ሰራ በበጎ ፈቃደኞች ትብብር የሰራ ቢሆንም ከፌዴራል፣ ኦንቴሪዮም ሆነ ከሲቲው ያገኘው ወይም የሚያገኘው ፈንድ እንደሌለ እና በኢትዮጵያ ኮሚኒት ትብብር እና የዩኒየን ተወካዮች ባደረጉት እርዳታ የሚቻለውን ሁሉ ያደረገ ቢሆንም፤ አሁንም በርካታ ሰደተኞች የመጠለያ፣ የቤትና የሰራ የማግኘት ችግር ያለባቸው መሆኑን እንዲሁም በአንዳንድ ሼልተር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ መሆኑንና በቅርቡም በዚህ አየር ጸባይ 6 ስደተኞች /ከሼልተር/መጠለያ አስወጥተዋቸው ማደሪያ አጥተው በስንት ውጣ ውረድ ሌላ መጠለያ ተገኝቶላቸው የገቡ መሆኑን ተነግሯቸዋል። የቶሮንቶ ሲቲም ለስደተኞች እርዳታ ወጪ ላወጡ ቤተክርስቲያንና ድርጅቶች የተወሰነ ወጪ እንተካለን ቢሉም፤ የኢትዮጵያ ማህበርን ቀደም ሲል ከሜይ መጨረሻ ጀምሮ እርዳታ ማድረግ የጀመረ ቢሆንም፣ ማመልከት የሚችለው ከጁላይ 17 ቀን 2023 በኋላ ብቻ ለወጣው ወጪ ነው በመባሉ፤ በማህበሩ ላይ አድልዎ የተፈጸመ መሆኑን እንዲሁም በስደተኞች ላይ በሺልተር አገልግሎት አሰጣጥ የማግለልና ዘረኝነት የተሰተዋለበት ሁኔታ መታየቱም ተነስቷል።

ክቡር ሚኒስትሩ ሁኔታውን በጽሞና አዳምጠው የችግሩን መጠን የተገነዘቡ መሆኑ አንስተው ከገንዘብ እርዳታ ውጭ ምን አይነት ሌላ እርዳታ ትፈልጋላችሁ? ብለው ለጠየቁት ጥያቄ፤ አንደኛ የቤት ማግኘት ችግር እንዲቃለል፣ ሁለተኛ የሰራ ማግኘት እና የኢምግሬሽን ፕሮሰሳቸው እንዲፋጠን በተለይም በደቡብ አፍሪካ በአደጋ ወስጥ የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ካናዳ በተፋጠነ ሁኔታ የሚመጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያም ሰላለው የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ላይ ግልጽ ጦርነት አውጆ ብዙ ሰላማዊ ሰዎች ያለቁበትና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስዎች ተፈናቅለው ባገኙት መንገድ ሁሉ ህይወታቸውን ለማዳን ከኢትዮጵያ በመሸሽ ላይ በመሆናቸው ይህም ወደፊት የስደተኞች ቁጥር እያሻቀበ ሊሄድ ሰለሚችል የካናዳ መንግሥት እንደዚህ አይነት ሁኔታ

በገጠማቸው አገሮች (ለምሳሌ በአፍጋኒስታን፣ ዩክሬን አሁን ደግሞ ሱዳን) አጣዳፊ እርምጃ በመውሰድ ሕዝቡን ለመታደግ እንደተቻለው፤ በኢትዮጵያስ ጉዳይ የካናዳ መንግሥት አጣዳፊ እርምጃ ለመውሰድ አላሰበም ወይ? ተብሎ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። የተከበሩ ሚኒስትሩም በተቻለ መጠን ግንዛቤ የወሰዱና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መልስ ሰጥተውበታል።

ወይይቱ በጥሩ ሁኔታ ተካሄዶ ሲያበቃ፤ ማህበሩ ያዘጋጀውን ቀለል ያለ ባህላዊ መክሰስ የቀረበ ሲሆን፤ ክቡር ሚኒስትሩም ወደ ኦታዋ ተመላሽ በመሆናቸው ለመታሰቢያ እንዲሆን አነስ ያለ ባህላዊ ሰዕሎች ያሉበት ስጦታ ተደርጎላቸው እና ከተሰበስቡት ጋር የመታሰቢያ ፎቶግራፎች ተነስተው እንዳበቃ፤ ክቡር ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ክብደት ሰጥተው ሰለመጡ የኢትዮጵያ ማህበር አመስግኖ፤ እንግዶቹም ሰለመስተንግዶው አመስግነው በክብር ተመልሰው ሄደዋል።

የኢትዮጵያ ማህበር በቶሮንቶና አካባቢው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል

ሜይ 28 ቀን 2023